ዕብ.11፡3. ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን፡፡
በሥጋዊ የስሜት ሕዋሳት መረዳት የማንችለው ዓለም በእርግጥ ይኖር ይሆንን ?
በእርግጥም በሥጋዊ የስሜት ሕዋሳቶቻችን መገንዘብ ከምንችለው በላይ፣ ራሳችንን ከምናውቀው በላይም ጭምር መንፈሣዊው ዓለም እርግጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም ቃል ይህንኑ ያረጋግጥልናል፡፡ የመክፈቻ ጥቅሳችንም ይህንኑ ይነግረናል፡፡ ማወቅና በጥልቀት መረዳት የፈለግን እንደሆነ በዙሪያችን እየተከናወኑ ያሉ ማናቸውም ጉዳዮች የራሳችንም እንቅስቃሴ ጭምር በመንፈሣዊው ዓለም የሚነዳ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ሰው የተፈጠረው እውነትና መንፈሥ ከሆነው ከኃያሉ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሰው መንፈሱ ከሥጋው ስትወሰድ የምናውቀው ሰው ሰው መሆኑ ይቀርና በድን ሬሣ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ለዛም ነው ሰዎች ሰውን ሲገድሉ የገደሉት ይመስላቸዋል እንጂ ገዳዮቹ በእርግጥ ያደረጉት ሥጋውን ወይም የመንፈሱ ማደርያ ሣጥኑን/ቀፎውን እውነተኛ ማንነቱ ከሆነው ከመንፈሱና ነፍሱ ነው እንዲለያይ ነው ያደረጉት፡፡ አንዴ ከተፈጠረ በኋላ የሰው መንፈሱና ነፍሱ ዘላለማዊ ናቸው፡፡ ሥጋዉም ቢሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አምኖ ዳግም የተወለደ መንፈሥ ያደረበት ከሆነ በዳግም ትንሣኤ የማይሞት ዘላለማዊና ባለክብር ሆኖ ይነሣል፡፡
ሰው በእግዚአብሔር አምሳል እንደ እግዚአብሔር መልክ ሆኖ ነው የተፈጠረው፡፡ ለዛም ነው አንድም ሦስትም የሆነው፡፡ ሰው=መንፈሥ+ነፍሥ+ሥጋ፡፡
ራሣችንንም ሆነ ሌሎችን መረዳት እንዲሁም ማስረዳት እጅግ ከባድ የሚሆንብን መንፈሣችንንና ነፍሳችንን በትንሹም ቢሆን መረዳት ሲያቅተን ነው፡፡ ራሣችንንም ሆነ ሌሎችን እጅግ ቀላልና በሥጋዊ አካላቶቻችንን ብቻ በመመልከትና በዓለማዊ እውቀት በመተንተን፣ በከንቱ ጥበብ በመጠበብ አሁን ያለንበት የእውቀት ጫፍ እየመሰለን ከሆነም ሥጋዊ የሥሜት ሕዋሳቶቻችን እየነዱን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ለዚህም ነው መንፈሣዊውን ዓለም በመጠኑም ቢሆን መረዳትና ባወቅነውም ልክ ወደ ተግባራዊ ጥበብ መሸጋገር ይጠቅመናል ብዮ የማስበው፡፡ መንፈሣዊውን ዓለም መረዳታችን የምናስበውንም ሆነ የምናደርገውን ነገር ስለሚቆጣጠረን በአካባቢያችን ልናስከትል የምንችለውን ተጽእኖ ለመቆጣጠር አንቸገርም፡፡ ወደ ውስጥ ማንነታችን ማለትም ወደ መንፈሣችን የምናስገባቸውንም ሆነ ከመንፈሣችን የሚወጡትን ማናቸውንም ድርጊቶችና አመለካከቶች መፈተን አንቸገርም፡፡
‘ሮሜ 12፡ 2. መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ’የተባልነውም ለዚህ ነው፡፡ ልክ አውሮፕላን ልንሣፈር ከመግባታችን በፊት ሁለት ሦስቴ ጓዛችን እንደሚፈተሸ ሁሉ ወደ ነፍሣችንና መንፈሣችን የምናስገባቸውን የአለምን ጓዞች፣ ኮተቶች፣ ድሪቶዎች፣ ጉድፎች ለማስቀረትና መልካም የሆነውን ብቻ ወደ ውስጠኛው ማንነታችን አስገብተን ሥጋችንንም ጭምር በሥርዐቱ ለማስገዛት ይህ ግድ ያስፈልገናል፡፡ አለበለዚያ ኮተት የበዛበት የክፉው መናፍስታዊ ዓለም መጫወቻዎች ልንሆን ተዘጋጅተናል ማለት ነው፡፡
መንፈሣዊ አረዳዳችንን ካስተካከልን ብቻ በእርግጥም በዙሪያችን የሚታየው ነገር በሙሉ ምንጩ ከማይታዮው መንፈሣዊ ዓለም መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ሰው=መንፈሥ+ነፍሥ+ሥጋ፡፡ በመሆኑም የራሱን መንፈሥ በመልካም ካሠለጠነ በእግዚአብሔር መንፈሥ የተሞላና እንደ ተፈጠረበት ፍፁም ዓላማ የፈጣሪዉ መልካም ባህሪ የሚንፀባረቅበት መልካም ሰው መሆን ይችላል፡፡ በዓለማዊ ሥነ-ምግባር መለኪያ ማለትም በስሜት ህዋሳቶች ብቻ የሚገለጽ አስመሳይ ትህትና ያለው ማለት ሳይሆን ከውስጠ-መንፈሡ የሚመነጭ እውነተኛ መልካም ሰው መሆን ይችላል ማለት ነው፡፡
መንፈሡን በክፋትና በማስመሰል ያሰለጠነ ሰው ግን በሰዎች መካከል ሲሆንና ብቻውን ሲሆን የሚያደርገው ድርጊት ፍፁም የተለያዮ ይሆናል፡፡ ከዛም ይባስ ብሎ አሁን በዘመናችን እንደምናዮው የዲያቢሎስ ተገዢ በመሆን የክፋት ምንጭ ይሆንና ሰውን ብቻ ሳይሆን ፍጥረታትንም በሙሉ የሚያስጨንቅ አስፈሪ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በርግጥ የእግዚአብሔር መንፈሥ ማደሪያ የሆነ ሰው ክፉን አይፈራም፡፡ ክፋት ራሱ ነው መፍራት ያለበት፡፡ ሰይጣን ራሱ፣ ግብረአበሮቹ ተባባሪ መናፍስቶችና ሰዎች ናቸው በፍርሀት መራድና መንቀጥቀጥ ያለባቸው ምክንያቱም የተዘጋጀላቸው የዘላለም የእሳት ባህር ፊት ለፊታቸው ነውና፡፡ ሰይጣን ምህረት የለውም፡፡ የሰው ልጅ ግን እስከመጨረሻዋ መንፈሡና ነፍሡ እስኪለያዩ ድረስ የምሕረት በር አልተዘጋበትም፡፡
በአጠቃላይ ለሥጋዊ የሥሜት ሕዋሣቶቻችን ሚሥጢራዊ የሆነውን መንፈሣዊው ዓለም በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች በመከፋፈል ከእግዚአብሔር ቃልና ካገኘኋቸው እጅግ ቁንጽል ከሆነው መንፈሣዊ መረዳቴ አንፃር ለማስቃኘት እሞክራለሁ፡፡
እነዚህም ሦስቱ ዋና ዋና ክፍሎች፡-
1. ቅዱሣን መናፍሥት፣
2. እርኩሣን መናፍሥት፣ እና
3. የሙታን መናፍሥት ናቸው፡፡
እያንዳንዱን ክፍል በሚገባ ተረድተን በመልካም የሕይወት ጎዳና በመነዳት እንደ እግዚአብሔር ፍፁም ዓላማ ፍፃሜያችን መልካም እንዲሆን መፈለግንም ማድረግንም በውስጣችን ይሞላን ዘንድ የጥበበ መንፈሥ ሁለመናችንን እንዲወርስ የሁላችንን ልብ ክፍት ይሁንልን፡፡
በሁሉም ነገር አምላኬና አባቴ መሪዮም የሆነው አስተማሪዮ መንፈሥ ቅዱሥ እንደሚረዳኝ በመተማመን ይሄንን ጉዳይ ጀምሬዋለሁ፡፡ በእግዚአብሔር ኃይል ለመልካም ፍፃሜ ይሆናል፡፡
I think it is good to know that. God Bless.
Thank you so much!