መግቢያ ጥያቄዎች፡-
ቅዱሳን መናፍስት ሁሌም የነበሩ ዘላለማዊ ናቸውን?
ቅዱሳን መናፍስት ይሞታሉን?
ቅዱሳን መናፍስት በቁጥር ስንት ናቸው?
አገልግሎታቸውስ ምን ይመስላል?
በዚህ ክፍል ውስጥ ቅዱሳን መናፍስት ብለን እንድናውቅ የፈለኩት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ ቅዱሳን መላእክትን ነው፡፡ የነዚህ ተቃራኒ የሆኑትን ደግሞ ኃጢአትን በራሳቸው ፈጥረው፣ ተንኮልን አቀናብረው የወደቁትን እርኩሳን መናፍስት ብለን እንጠራቸዋለን፡፡
ስለዚህ ቅዱሳን መላእክት ቅዱሳን ሆነው ሳይረክሱና ሳይቆሽሹ እግዚአብሔርን እያመለኩና እያገለገሉ ያሉ እልፍ አዕላፋት ቅዱስ ፍጡራን ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በትዕቢትና በሀሰት የዓላማ ቀመር ተነሳስተው ከመንበራቸው የተዋረዱ ” የውሸት አባት” የተባለው ሳጥናኤል እየመራቸው ዓለሙን ሁሉ በማሳሳት በርኩሰት እየነዱት ያሉ እርኩሳን መናፍስት ይገኛሉ፡፡
ለመሆኑ ”መልአክ” የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? በዜና መዋዕል ካልዕ መጽሐፍ ያለውን ቃል ብንመለከት ትርጉሙን ያብራራልናል፡፡
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ፣ ምዕራፍ 32፡
20. ንጉሡም ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ጸለዩ፥ ወደ ሰማይም ጮኹ።
21. እግዚአብሔርም ጽኑዓን ኃያላኑንና መሳፍንቱን አለቆቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር እንዲያጠፋ መልአኩን ሰደደ።
የዚህን ተመሣሣይ ቃል በትንቢተ ኢሣይያስም ላይ እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን፡-
ትንቢተ ኢሳይያስ 37፡
36 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ።
ከላይ በተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ነቢዩ ኢሳይያስና ንጉሡ ሕዝቅያስ ከአቅማቸው በላይ በሆነባቸው ጦርነት ምክንያት ወደ እግዚአብሔር ጮሁ፣ ጸለዩ፡፡ እግዚአብሔርም ለጸሎታቸው መልስ የጠላቶቻቸውን ጦር ሙሉ በሙሉ ይደመስስላቸው ዘንድ አንድን መልአክ ሰድዶ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ የሚሆነውን የሰለጠነ የጠላት ጦር ሙሉ በሙሉ ደመሰሰላቸው፡፡
በዚህም ማስረጃ መሠረት መልአክ የሚለው ቃል በነጠላ ትርጉሙ መልእክተኛ፣ አምባሳደር፣ አንድን ተልዕኮ እንዲፈጽም የተላከ፣ አንድን መልእክት እንዲያደርስ የተላከ፣ በተለይም ከእግዚአብሔር አምላካችን የተላከ ሰማያዊ መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ከ200 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡
በብሉይ ኪዳን መላእክት በብዙ ቦታ ላይ ተጠቅሰዋል፡፡ የቀደሙ ፓትርያሪኮችን ማለትም ከአዳም ጀምሮ፣ አቤልን፣ ሄኖክን፣ አብርሐምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዮሴፍን፣ ወ.ዘ.ተ. እንዲያግዙ ወይም ለነሱ መልእክት እንዲያደርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከዋል፡፡ በተመሣሣይም ለበለዓም፣ ለዳዊት፣ ለነቢዩ ዘካርያስ፣ ለሌሎችም እንዲያግዟቸውና መልእክት እንዲያደርሱ ተልከዋል፡፡ ለቅድስት ድንግል ማርያምም እንዲሁ የብሥራት መልዕክተኛ ብለን የምናውቀው ቅዱስ መልአኩ ገብርኤል ብስራትን አብስሯታል፡፡ ይሄንንም በተለምዶ የገብርኤል ብስራት ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡
በነገራችን ላይ የዘመናችን መሪዎች ሕዝቅያስና ኢሳይያስ ያደረጉትን፣ ሁለቱ ብቻ የተገበሩትን አይነት ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በእውነተኛ መንፈሥ ቢጮሁ በሀገር ውስጥም ይሁን ከውጪ እየሆነ ያለውንና ሊመጣም ጭምር ያለውን የክፋትና የተንኮል እንዲሁም የግፍ አረመኔነት አንዱ ባንዱ ላይ የመስፋፋትና የስግብግብነት ወረራ እንደ እግዚአብሔር ሀሳብና እንደ መሪዎቹ ንጹህ ልብ እንዲሁ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እንደነገሩ በማስመሰልና በውሸት ሳይሆን ከእውነትና ከመንፈሥ የሆነውን የጸሎት ጩኸት ወደ እውነተኛውና መንፈሥ ወደ ሆነው ኃያሉ እግዚአብሔር ማለቴ እንጂ በዲሞክራሲያዊ እጅ ብልጫ አይነት እውነትን ገድሎ የመቅበር የሚመስል የሹፈት ጸሎት ወዲህም ወዲያም…ማለቴ አይደለም፡፡ የሀሰት ጸሎት ውጤትንማ ንጹሐኑ እየተጎነጩት፣ የሕዝብ ተወካይ ተብዮዎቹ እንደሚያደርጉት የአፍ በራቸውንም ጭምር ክፍት በር አልባ እያደረጉት፣ የኃይማኖት ተቋማት ሙታናቸውን እየቀበሩ፣ በማያባራ ሽክርክሪት ያለውን ኡደት እንደጉድ እየገረመምነው ነው፡፡
እግዚአብሔር ግን ዛሬም ህያው ኃያል አምላክ ስለሆነ ብንለምነው ይሰማናል፡፡ ለምነንም መልሱን መቀበል እንችላለን፡፡ ትላንት በግፍ የሞቱትን የሙታን መናፍሥት የደምና የነፍስ ጽዋ እንዲበቀሉ ኃያላን መላእክቱን እንዲያሠማራ እግዚአብሔርን በመንፈሥና በእውነት ከጠየቅን ይሆንልናል፡፡ አንዱ የእግዚአብሔር መላአክ ብቻ በሁለት ታማኝ ሰዎች ጸሎት 185000 የሠለጠኑ ኃያላን የሰው ሠራዊትን መቅሰፍ ከቻለ፣ 10 እውነተኛ ጸሎተኞች በምድራችን ቢኖሩና እንዲሁ ቢደረግላቸው ብለን ብናስብ…….
ለነገሩ ለያንዳንዳችን የተመደቡትን ጠባቂ መላእክት ብናስተውል አንድ ሰው ብቻ ምን ያህል አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ማወቅ እንችል ነበር፡፡ በቀጣይ ይኼንን ጉዳይ በስፋት እመለስበታለሁ፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዳችንን በእውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ማስታጠቅ የእግዚአብሔር ፍጹም ዓላማ ነው ብዮ ስለማስብ፡፡
ትንቢተ ሆሴዕ፣ ምዕራፍ 4፣ ቁጥር 6 ላይ” ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ።” የሚለው እንዳይፈፀምብን በዚህ ቃል መሠረት እምነት ሞልቶ ተርፎ እውቀት ማለትም እግዚአብሔርን ማወቅ ከታጣ እሱም የጥፋት ጎዳና መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋልና ነው፡፡
በመጨረሻም ሁሉም መላእክት ቅዱሳን መላእክት እንዳልሆኑ ሁላችንም የምንረዳው ሀቅ ቢሆንም ተጨማሪ ማብራሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ጥቅሶችን እነሆ፡-
መጽሐፈ ምሳሌ 16፡ 14 የንጉሥ ቍጣ እንደ ሞት መልእክተኛ ነው፤ ጠቢብ ሰው ግን ያቈላምጠዋል።
የሞት መላእክት አሉ ማለት ነው፡፡
መዝሙረ ዳዊት 78፡ 49 የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ፤ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ::
ክፉ መላእክትም ይላካሉ፣ ይታዘዛሉ ማለት ነው፡፡
መጽሐፈ ምሳሌ 17፡11 ክፉ ሰው ዓመፃን ብቻ ይሻል፤ ስለዚህ ጨካኝ መልአክ ይላክበታል።
ጨካኝ መላእክም ሊላክ ይችላል ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሔር መላእክትን ልዕለ-ተፈጠሯዊ ባሕሪ ሲያስረዳ ደግሞ መዝሙረ ዳዊት 104፡ 4 ”መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል። ” ይለናል፡፡
ለዚህም ነው በተለይ መንፈሣችንን በእግዚአብሔር እውነት፣ ጥበብና እውቀት ማበልጸግ የሚጠበቅብን፡፡ ዓለማዊ ብልጽግና እንደ አንዲት የህይወት ቅርንጫፍ ዋና ያልሆነ ተጨማሪ ጉዳይ ሲሆን በመንፈሣዊ ግንዳችን የበለፀግን ከሆነ ሥጋዊ ብልጽግናውን የምንደርሥበት እውን የምናደርግበት ሆኖ የእግዚአብሔርን ዓላማ በአግባቡ ካልተረዳነው ግን የሌሎችን ቅራቅንቦና ኮተት፣ የሰይጣንንም ጭምር ስለምንኮትት አጓጉል ሆነን ሌሎችንም አጓጉል እንዳናደርግ መጠንቀቅ አለብን፡፡
በቀጣይ የቅዱሳን መላእክትን ባህሪ እና አገልግሎት በስፋት እንቃኛለን፡፡
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡ 14 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።